የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በካናዳ 30ኛ ዓመታዊ የመሪዎች ስብሰባንና የሕብረቱን ዋና ጸሐፊ አገልግሎት ማስጀመር አስመልክቶ የተዘጋጀ ልዩ ኮንፈረንስ
በካናዳ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት 30ኛ ዓመታዊ የመሪዎች ስብሰባ ካለፈው ሰኞ ሴፕቴምበር 18 ቀን ጀምሮ በFair Havens Camp & Conference Centre Beaverton, Ontario L0K 1A0 Canada የቀጠለ ሲሆን ስብሰባው የፊታችን ዐርብ ሴፕቴምበር 22 እኩለ ቀን ላይ ይጠናቀቃል፡፡
በመቀጠልም በቶሮንቶ የሚገኙት በካናዳ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት አባል አብያተክርስቲያናት አዘጋጀነት የተዘጋጀው የሁለት ቀናት ኮንፈረንስ በቶሮንቶ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ይደረጋል፡፡
ዐርብ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ በቃል የሚያገለገልት ፓስተር መልኬ ነጋሽ በዊኒፔግ የሕያው ወንጌል ቤተክርስቲን ዋና መጋቢና የወቅቱ የሕብረቱ ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
ቅዳሜ የወቅቱ የሕብረቱ ቦርድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ፓስተር ወርቅነህ ሞገሴ በካልጋሪ የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢና ፓስተር ተረፈ ሰረቀ በኤድመንተን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢ ኮንፈረንሱን በቃል ያገለግላሉ፡፡
በመጨረሻም ዕሁድ ሴፕቴምበር 24 ቀን 2023 ዓመተ ምሕረት በቶሮንቶ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ጉባኤ ላይ በካናዳ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረትን በዋና ጸሐፊነት ለማገልገል በቅቡ ከኖርዌይ ወደ ካናዳ ለመጡት ለፓስተር ዮሐንስ ተፈራና ለባለቤታቸው ለእህት አሰለፈች አሰፋ በጉባኤ በመጸለይ ኃላፊነቱን የማስረከብ ሥነ-ሥርዓት ይደረጋል፡፡
በዕለቱ የእግዚአብሔርን ቃል በማቅረብ የሚያገለግሉት ፓስተር ቻላቸው እሸቱ በካልጋሪ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢና የወቅቱ የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡
በ30ኛው የሕብረቱ አመታዊ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ከመላው ካናዳ የተገኙ መጋቢዎችና የቤተክርስቲያን መሪዎች በቶሮንቶ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ገባኤ ላይ በመገኘት ለፓስተር ዮሐንስ ተፈራና ለባለቤታቸው ለእህት አሰለፈች አሰፋ በሕብረት በመጸለይ የፕሮግራሙ ፍጻሜ ይሆናል;;
በዚህ አጋጣሚ በካናዳ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ስር አስፈጻሚ ኮሚቴ ይህ 30ኛ ዐመታዊ ስብሰባ እንዲሳካ ያልተቆጠበ ጥረት ያደረጉትን በቶሮንቶ ከተማ የሚገኙትን አባል ቤተክርስቲያናትና ኮንፈረንሱን በማስተናገድና ለጉባዔው ተሳታፊዎች በራቸውን በመክፈት ያልተቆጠበ ድጋፍ ላበረከቱት እንዲሁም ለሕብረቱ ዋና ጸሐፊ የሚሆን ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት በማዘጋጀት ለተባበሩት በቶሮንቶ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
በመጨረሻም ለሕብረቱ 30ኛ አመት የመሪዎች ስብሰባ በቤተክርስቲያን አመራርና በመሪዎች ሚና ዙሪያ ጠቃሚ ትምሕርት ያስተማሩትን ፓስተር በድሉ ይርጋን በዳላስ ቴክሳስ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ባፕቲስት ቤተክርቲያን ዋና መጋቢን እግዘአብሔር አብዝቶ ይባርክዎ እንላለን፡፡