News and Updates

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በካናዳ ዋና ጸሐፊ ሾመ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በካናዳ ዋና ጸሐፊ ሾመ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በካናዳ በመላው አገሪቱ ውስጥ  የሚገኙትን የሕብረቱን አባል አብያተ ክርስቲያናትን  የዕለት ተዕለት ተግባራት በማስተባበር፣ ውሳኔዎችን በመከታተልና በማስፈጸም ረገድ ትልቅ እርምጃ ለሚጠበቅበት ለሕብረቱ የዋና ጸሐፊነት የስራ ኃላፊነት ፓስተር ዮሐንስ ተፈራን ሾሟል፡፡


በካናዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን  አብያተ ክርስቲያናት ማሕበረሰብ በፓስተር ዮሐንስ ተፈራ  መሪነት በታላቅ ጉጉት  በሕብረቱ ታሪክ ውስጥ የአዲስ ዘመን መባቻን ይጠብቃል።
ፓስተር ዮሐንስ ተፈራ ከ20 አመታት በላይ በኖርዌይ የቤተክርስቲያን መሪና መጋቢ ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ በኢትጵያውያን መካከል ከመጀመሪያዎቹ አንዱ የሆነውን ፓልቶክ በተባለ ማሕበራዊ ሜዲያ በኢንተርኔት  የወንጌል  አገልግሎት በማቋቋም በመላው ዓለም የተበተነው ሕዝባችን የእግዚአብሔር ቃል እንዲደርሰው አድርገዋል፡፡አሁንም ይህ አገልግሎት በሳምንት ሰባት ቀናት  በቀን 24 ሰዓታት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህም አገልግሎት አማካይነት በርካታ ነፍሳት ጌታ የሱስ ክረስቶስን አግኝተው  እንዲድኑ፣ ከዕምነታቸውና ከአገልግሎት ኃላፊነታቸው  የደከሙ እንደገና ተጽናንተውና ተበረታትው ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ፣ በሕመም ይሰቃዩ የነበሩ እንዲፈወሱና የሕክምና ዕርዳታም ጭምር እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም መረብ የተባለ ዓለም አቀፍ ስርጭት ያለው በየ3 ወሩ እየተዘጋጀ የሚወጣ መንፈሳዊ መጽሔት በማዘጋጀትና በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በማሰራጨት ብዙዎችን በወንጌል ደርሰዋል፡፡


ፓስተር ዮሐንስ ተፈራ አዲሱን የስራ ኃላፊነት ለመረከብ ወደ ካናዳ እስከመጡበት ጊዜ ድረስ በኦስሎ ኖርዌይ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢ  የሰሜን አውሮፓ ወንጌላውያን አብያተ ከርስቲያናት ሕብረት ሰብሳቢ  ፣ የኖርዌይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወንጌላውየን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ዋና ጸሐፊ፣ በአውሮፓ ኢትዮጵያውያን ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መጋቢዎች ሕብረት ዋና ጸሐፊና በመሆንና በሌሎችም በርካታ የአገልግሎት መስኮች  እያገለገሉ ነበር፡፡


የፓስተር ዮሐንስ ልዩ የአመራር ክህሎት ከማሕበረሰቡ ፍላጎት ጋር ካለው ጥልቅ ፍላጎትና ክፍተት  ጋር ተዳምሮ ለውጥ በማሳየት በካናዳ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን ራዕይና ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ  ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽእኖና ድጋፍ  ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።