ለነፍሴ ሰላም አላት ! It is well with my soul !
ለነፍሴ ሰላም አላት ! It is well with my soul !
ሆራቺዮ ስፓፈርድ የተባለ ታዋቂ ሃብታም ነጋዴ በ 19ኛውክፍለ ዘመን በአሜሪካን አገር በቺካጎ ከተማ ይኖር ነበር፡፡ ሆራቺዮ ስፓፈርድ በተማዋ ታዋቂ ሃብታም ብቻ ሳይሆን ታዋቂ የወንጌል አማኝና አገልጋይ ነበር፡፡ በአሜሪካ የመነቃቃትና የከፍተኛ የወንጌል ንቅናቄ ውስጥ ተሳታፊ ከመሆንም አልፎ በወቅቱ በአሜሪካና በአውሮፓ ታላቅ ዝናን ያተረፈው የድዋይት ላይማን ሙዲ (Dwight L. Moody) ዲ.ኤል. ሙዲ መባልም የሚታወቀው፣ የሙዲ ቸርችን፣ የኖርዝፊልድ ትምህርት ቤትን እና የማውንት ሄርሞን ትምህርት ቤትን በማሳቹሴትስ፣ ሙዲ ባይብል ኢንስቲትዩት እና ሙዲ አሳታሚዎችን የመሰረተ አሜሪካዊ ወንጌላዊ እና አሳታሚ ነበር።
የሆራቺዮ ስፓፈርድ ቤተሰብ ቺካጎ ውስጥ በተከሰተ ተላላፊ በሽታ ወንድ ልጃቸውን በሞት ተነጠቁ፡፡ ከዚያም መሪር ሃዘን ቤተሰቡ ገና ሳያገግም ሌላ አሳዛን መከራ በቤተሰቡ ላይ ወደቀ፡፡ ይህም አደጋ በአሜሪካም ሆነ በቺካጎ ከደረሱት የእሳት አደጋዎች ሁሉ ከፍተኛው የሆነው ታላቁ የቺካጎ እሳት ቃጠሎ ተብሎ የሚታወቀው አደጋ የቺካጎን ከተማ የንግድ ማዕክል በማጥቃት የከተማዋ የንግድም ማዕከሎች ሲወድሙ የሆራቺዮ ስፓፈርድ ንብረትም አብሮ ወደመ፡፡
በዚህ ወቅት ከላይ ስሙን የገለጽነው ዲ.ኤል ሙዲ የተባለው ታዋቂ አገልጋይ በወቅቱ ከአሜሪካ ወደ እንግሊዝ አገር ሄዶ በማገልገል ላይ ነበር፡፡ ሙዲና ሰፓፈርድ ደግሞ የተቀራረቡ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ስፓፎርድ ከዚህ ከደረሰበት ተደጋጋሚ ሃዘንና መከራ ለማገገም ወደ እንግሊዝ አገር ሄዶ በዚያ በማገልገል ላይ የሚገኘውን ጓደኛውን ዳዊት ሙዲን እያገዘ የተወሰነ ጊዜ ለማሳለፍ ቤተሰቡን ይዞ ሄዶ ትንሽ ተጽናንተው በዚያውም እንግሊዝ አገርን ጎብኝተው ለመመለስ ወስነው ዝግጅት ጀመረ፡፡
ወደ እንግሊዝ አገር ለመጓዝ የወሰኑበት ቀን ደርሶ ጓዛቸውን አዘጋጅተው ከቤት ሊወጡ እየተዘጋጁ እያሉ የማዘጋጃ ቤት ተላላኪ በር አንኳኳ፡፡ ተላላኪውም “ በከተማው በቅርቡ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ስለወደመው ንብረትና ካሳ ሁኔታ ለመነጋገር በሚቀጥለው ሳምንት ወሳኝ ስብሰባ ስለተጠራ በስብሰባው እንዲገኙ መልዕክት እንድነግርዎ ተልኬ ነው” አለው
ሚስተር ስፓፎርድም መልሶ “ እንዴ እኔ በጪራሽ አልችልም ፡፡ አሁን ወደ እንግሊዝ አገር ለመጓዝ ከነቤተሰቤ የመርከብ ትኬት ቆርጨ ከቤት ልወጣ ስል ነው የደረስከው ” አለው፡፡
ተላላኪውም “ ሚስተር ስፓፎርድ እርስዎ የሚያዋጣዎትን ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስብሰባ ስለወደመው ንብረት.፣ በቃጠሎው ምክንያት ስለተመሰቃቀለው የድንበርና ቦታ ይዞታ ፣ ስለ ሱቆች ቦታ አከላልና ስለመሳሰሉት ወሳኝ ጉዳዮች ውሳኔ የሚሰጥበት ስብሰባ ነው፡፡ ውሳኔውን ለእርስዎ እተዋለሁ ብሎ ሰላምታ ሰጥቶት ሄደ፡፡
ሚስተር ስፓፎርድ ከባለቤቱ ጋር ስለሁኔታው ጥቂት ከተወያየ በኋላ “ በቃ አንቺና ልጆቹ ቀድማችሁ ሂዱ ፡፡ አኔ ስብሰባውን ጨርሼ በኋላ እመጣለሁ” ብሎ ባለቤቱንና አራት ሴት ልጆቹን በመርከብ አሳፍሮና ሸኝቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
ከ3 ቀናት በኋላ የጽሕፈት ቤት በሩ ተንኳኩቶ የቴሌግራም መልዕክተኛ አንድ መልዕክት በእጁ ሰጠው፡፡ ቴሌግራሙን ከፍቶ ሲያነበው saved alone! የሚል ነበር፡፡ ቤተሰቡ የተጓዘባት SS (Steam Ship) Ville du Havre, የተባለችው መርከብ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ከሌላ መርከብ ጋር ተጋጭታ በመስጠሟ አራቱም ልጆቹ መስጠማቸውን ለመግለጽ ባለቤቱ የተጠቀመችው ቃል “ እኔ ብቻ ቀርቻለሁ” saved alone! የሚል መልዕክት ነበር፡፡
ወንድም ሆራቺዮ ስፓፎርድ በአጪር የጊዜ ልዩነት ወንድ ልጁን በበሽታ ፣ ንብረቱን በእሳት አደጋ ፣ 4 ሴት ልጆቹን በባሕር ስጥመት ሲያጣ ምን ዓይነት ጥልቅ ሃዘን እንደሚሰማው መገመት ቀላል አይደለም፡፡ የሚገርመው ሆራቺዮ ራሱ አገልጋይና የሙዲ የቅርብ ረዳት የነበረ ሲሆን እንደውም የሙዲን አገልግሎት በገንዘብ የሚደግፍ እንደነበረ ይነገራል፡፡
ከዚያም በደረሰብት ሃዘን እየተኮማተረ እንግሊዝ አገር ብቻዋን ሃዘን ላይ ከምትገኘው ባለቤቱ ጋር ለመሆን በሌላ መርከብ ተሳፍሮ ጉዞ ጀመረ፡፡ ጉዞውም እንደተጀመረ የመርከቡን አስተናጋጅ SS Ville du Havre የሰመጠችበት ቦታ ሲደርስ እንዲነግረው አደራ ብሎ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ አንድ ቀን አስተናጋጁ ክፍሉን አንኳኩቶ “ ሚስተር ስፓፎርድ በትክክል ቦታውን ይህ ነው ማለት ባይቻልም Ville du Havre የተባለችው የንግድ መርከብ የሰመጠችው እዚህ አካባቢ ነው” አለው፡፡.
ሚስተር ስፓፎርድም መርከቡ በረንዳ ላይ ሆኖ ያንን ከባሕር እየተምዘገዘገ እየመጣ መርከቡ ላይ እየተላተመ የሚያልፈውን አረፋ እያየ ለብዙ ሰዓታት እየተንሰቀሰቀ ጌታ ሆይ ለምን ? Why God? እያለ በሃዘን ቆዬ፡፡ ከዚያም ወደ ጥልቁ ባሕር አተኩሮ ሲመለከትና ሲተክዝ ድንገት በባሕሩ የማዕበል አረፋ ውስጥ ” እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ “ የሚለውን ቃል መንፈስ ቅዱስ በአዲስ ኃይልና መገለጥ ወደ ልቡ አመጣ፡፡
ሚስተር ስፓፎርድም ፊቱ በድታና ሃዘንን በሚያስረሳ መንፈስ ተሞልቶ ” ኦ ጌታ ሆይ! ለካ አንተም ልጅን በሞት ማጣትና ሃዘን ምን እንደሆነ ታውቀዋለህ “ በማለት መንፈሱ መጽናናት ጀመረ፡፡ በዚህ ቃል በመጽናናት ጥልቅ እምነቱና በእግዚአብሔር ላይ ያገኘው ሰላም ከሐዘንም ከደስታም በላይ እንደሆነ አረጋገጠ፡፡ ከዚያም በጉዘው መጨረሻ ዛሬ በመላው አለም እጅግ ታዋቂ፣ ዝነኛ ፣ ተወዳጅና አጽናኝ የሆነውን It is well with my soul ! “ለነፍሴ ሰላም አላት “ የተባለውን መዝሙር ደረሰ፡
የመጀመሪያው ስንኝ እንደዚህ ይነበባል፡፡
" ሰላም እንደ ወንዝ በመንገዴ ላይ ተትረፍርፎ ሲፈስ
ደግሞም ሃዘን እንደ ባሕር ማዕበል ዙሪያዬን ሲያጓራ ;
ዕጣዬ ምንም ይሁን ምን፣
ለነፍሴ ሰላም አላት እንድል አስተምረኸኛል፣
ለነፍሴ ሰላም አላት፣ ለነፍሴ ሰላም አላት ፡፡
It is well with my soul
When peace like a river, attendeth my way,
When sorrows like sea billows roll;
Whatever my lot, Thou hast taught me to say,
It is well; it is well, with my soul.
ሚስተር ስፓፎርድ በ1828 ዓመተ ምሕረት ኒው ዮርክ ውስጥ ተወልዶ በ1888 ዓመተ ምሕረት በተወለደ በ60 አመቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ የሞተ አሜሪካዊ ሲሆን ይህ ሁሉ መከራ ሲፈራረቅበት የ43 ዓመት ጎልማሳ ነበር፡፡ ጌታ ዛሬ በሐዘንና በመከራ ውስጥ የምታልፉ ሁሉ ይህ ሐዘን ያልፋል፡፡ ለቅሶና ሃዘን የሌለበት ጨለማ የማይኖርበት የዘላለም ሕይቀትን ተስፋ የምተደረጉ ሁሉ አይዟችሁ ይህም ያልፋል፡፡
ይህ መዝሙር ላለፉት 200 ዓመታት የብዙዎች መጽናኛ ሆኖ እኛ ጋር ደርሷል፡፡ ሙሉውን መዝሙር ይህን ቅጥያ በመጫን ስሙት፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=rhaTIu_k4w0