ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት - (ዘፍጥረት 4፥7) Girma Bekele (Phd)Pastor
ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት - (ዘፍጥረት 4፥7)
በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራትና በአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገራት (OACPS) መካከል በ 403 ገጾች የተካተተ ለ 20 ዓመታት የሚዘልቅ ታሪካዊ የአጋርነት ስምምነት (OACPS-EU Partnership Agreement, 15 November 2023) በ አፒያ ሳሞዐ ተፈርሟል። ስምምነቱ ከ 20 ዓመት በፊት በኮትኑዩ፤ ቤኒን የተፈረመውን ስምምንት (The Cotonou Agreement, 23 June 2000) የሚተካና፣ በስድስት አንኳር ጕዳዮች ላይ አሳሪ መርሕ ይሆናል። እነዚህም ሰብአዊ መብቶች፣ ዲሞክራሲና አገረ መንግሥት፣ ሰላምና ደኅንነት፣ የሰውና የማኅበራዊ እድገት ልማት፣ ዘላቂ የተፈጥሮ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የሰው ፍለሰት እና እቅስቃሴን በተመለከተ ነው።
ከፍ ሲል በተጠቀሱት የስምምነት ነጥቦች ላይ ያለኝ ግንዛቤ ከአጠቃላይ ዕውቅት ያለፈ አይደለም። ስምምነቱ ለአገራችን ያለውን ፋይዳ፣ ዝርዝር ትንተናና እንድምታ ለባለሙያዎቹ እተዋለሁ። ሆኖም አስፈላጊነቱን በጽኑ አምናለሁ። ትኵረቴ ሰብ አዊ መብትንና አካታችነትን ተንተርሶ በቀረበው የጾታ ማንነትና የወሲብ እሳቤ ላይ ነው። እጅግ አሳሳቢና የማኅበረሰብን በተለይም የጾታ ማንነትን፣ የወሲብ ትምህርት፣ የጋብቻንና የቤተ ሰብን መሠረት ከሥሩ የሚያናጉ ፖሊሶዎችን ይዟል። ይህን አስመልክቶ ያስተዋልኳቸውንና ትኵረት የሚሻቸውን የስምምነቱን ነጥቦች በአምስት በመክፈል እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
1) ያልተገደበና አካታች የጾታ ማንነትን “የሚያከብር” ሰብአዊ መብት ተግባራዊ ማድረግ
ባለ ደርሻ አካላት፣ ማለትም በአንድ ጐራ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት፣ በሌላኛው ጐራ አፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገራት፣ “ለሰብአዊ መብቶች” መከበር በጋራ እንደሚሠሩ በአጽንዖት ተሰምሯል። በተለይም የተባበሩትን መንግሥታትና የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት (OECD) መርሖች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው የሚያግዙ ፖሊሲዎችና ደንቦች፣ በግል፣ በማኅበራዊና በባህል ዘርፉ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ማረጋገጥ ነው። ይህም ማለት በሥራ ላይ ያሉት የአገራት ፖሊሲዎች፣ ድንጋጌዎችና ደንቦች በዚህ አግባብነት በየጊዜው ይቃኛሉ (አንቀጽ 2፣ ቍ. 5፤ አንቀጽ 4፣ ቍ. 1፤ አንቀጽ 9፣ ቍ.2፤ አንቀጽ 13፣ ቍ. 5፤ አንቀጽ 20፤፣ ቍ. 5)።
እንደሚታወቀው ከ 38ቱ የ OECD አገራት 24ቱ የግብረሰዶም ጋብቻን ያጸደቍ.፣ እንዲሁም የድርጅቱ የውጪ እርዳታ ፓሊሲ ይህንኑ አካታች እንዲሆንና ተረጂ አገራትም “በሰብአዊ መብት” ሰበብ እንዲቀበሉት ጫና ያደርጋሉ። በአገራች ሰላም፣ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነትትና ሰብአዊ መብቶች መከበረ የወቅቱ የአገራችን ዐቢይ ጥያቄዎች ናቸው። ሆኖም ስምምነቱ የሚጥይቀው “ያልተገደበና አካታች የጾታ ማንነት መብት” ችግራችን አይደለም። ቢያንስ የአብዛኛው ሕዝብ።
2) የምዕራቡ ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም (Gender Ideology) ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ
ስምምነነቱ እ. ጐ. አ በ 2030፣ ድኽነትን ማጥፋት፣ ጾታዊ አድሎአዊነትን ማስቀረትና የጾታ [Gender] እኩለነትን ማረጋጥ ግብ ያደርጋል። ለዚህም አፈጻጸም ይረዳ ዘንድ፣ ባለ ደርሻ አካላት በኅብረተሰባቸው መካከል ያሉ “የተዛቡ የጾታ ዕይታዎችን” ማስተካከል፣ እንዲሁም የጾታን ማንነትን፣ መብትንና እኩልነትን በተመለከተ በፓሊሲዎችና በፕሮግራሞች ሁሉ ውስጥ ማስረጽና ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋል። (አንቀጽ 2፣ ቍ. 5፤ አንቀጽ 9፣ ቍ. 2፤ አንቀጽ 10፣ ቍ. 1፤ አንቀጽ 41፤ አንቀጽ 80፣ ቍ. 3)።
ለመሆኑ የምዕራቡ ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም በአጭሩ ምንድነው?
የዚህ ርዕዮተ ዓለም “የወሲብ አብዮት አባት” በመባል የሚታወቀውና ከዚህም ጋር ተያይዞ የምዕራቡን ዓለም የጾታና የወሲብ ግንዛቤ፣ ዕሴቶችና ባህል ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የቀየረው የኢንዲያናው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አልፈርድ ሲ ኪንዚ (June 23, 1894 — August 25, 1956) ነው። በተለይም “የኪንዚ ሪፖርት” በመባል የሚታወቍት Sexual Behavior in the Human Male (1948) እንዲሁም Sexual Behavior in the Human Female (1953) “የምርምር ሥራዎች” ለምዕራቡ ዓለም ወሲባዊና የጾታ ማንነት ቀውሶች ትልቅ አስተዋጾኦ አድርገዋል።
ሁለተኛው ሰው ትውልደ ኒውዚላድ የሆነ አሜሪካዊው ጆን መኒ (8 July 1921–7 July 2006) ነው። መኒ በጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ታዋቂ የሕፃናት ሕክምናና የሥነ ልቡና ፕሮፌሰር ነበር። በግብረ ሰዶም ወታደራዊ አራማጆች ዘንድ “የጾታ ለውጥ ንቅናቄ መንፈሳዊ አባት (the spiritual father of trans movement)” በመባል ይታወቃል። በምዕራቡ ዓለም ያለው “የጾታ ለውጥ” ሕክምና ሳይንሳዊ ፍልስፍና መሠረት ያረፈው በዚሁ በጆን መኒ ሥራዎች ላይ ነው።
“ጾታ ተፈጥሮአዊ ሳይሆን” ማኅበራዊ ውቅር (social construct)” ነው የሚለው የጾታ ርዕዮተ ዓለም (Gender Ideology] ፊት አውራሪ ነበር። መኒ “ወንድነትም ሆነ ሴትነት” ምርጫና ማኅበራዊ ውቅር እንጂ ተፈጥሮአዊ አይደለም የሚል ጽኑ እምነት ነበረው። ልጆች ጾታ “ገለልተኛ ሆነው እንደሚወለዱ” (born gender neutral)፣ ምንም ተጽዕኖ በማያመጣ መልኩ “ጾታቸውን” በሕክምናና በቴራፒ መቀየር እንደሚቻል ይሞግታል። በ1965 በአሜሪካ ያቋቋመው የመጀመሪያው የጾታ ዝውውር ቀዶ ጥገና (sex reassignment surgery) የሕክምና ፍልስፍና መሠረት ይኸው የተጣመመ ግንዛቤ ነበር። ኪንዚም ሆነ መኒ በወሲብ ጕዳይ በራሳቸው እጅግ ግራ የተጋቡ፤ ከሁለቱም ጾታዎች፣ እንዲሁም የጾታ ለወጥ ካደረጉ ጋር ክፍትና ያልተቆጠበ ግኑኙነት ነበራችው።
የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች (UN Women) የሰብአዊ መብቶች ሙግት መሠረት ያረፈው በኪንዚና በመኒ ሥራዎች ላይ ነው። ለምሳሌ፣ “ጾታ [ወንድነትና ሴትነት] ሥነ-ተፈጥሮአዊ ሳይሆን” ማኅበራዊ ውቅር (social construct) በመሆኑ በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነ ብዙ ዐይነት መገለጫዎች አሉት” (UN Women: United Nations Entity for Gender Equality) የሚል ጽኑ እሳቤ አለው። በአሁኑ ወቅት በምዕራቡ ዓለም አተርጓጐም “ጾታዊ ማንነቶች” እስከ 107 ደርሰዋል። በዚህም አያበቃም። በዚህ ስምምነት ውስጥ የተሰወረው “ሰይጣን” የእነዚህ ሁለት ሰዎች ሥራ ነው። ቅዱስ ቃሉ እንደሚለው “ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው፤” (ዘፍ 1፥27)። ወንድ እና ሴት እኩል ናቸው፤ አንድ ዐይነት ወይም ተለዋዋጭ ግን አይደሉም። የማኅበረ ሰብ መሠረት ቤተ ሰብ ነው፤ የቤተ ሰብ መሠረት “የወንድ እና የሴት” እኩልነትና ጾታዊ ልዩነት ነው። በዚህ ስምምነት አማካኝነት “በሰብአዊ መብትን” በመንተራስ ይህን ዘላላማዊ እውነት የሚያፈርስና የቤተ ሰብን፣ የማኅበረሰብንና የአገርን መሠረት የሚናጋ ዕቅድ ወደ አገራችን እየመጣ ነው። እናስተውል፤ እንንቃ! ድኽነትን በጋራና በትጋት እየተዋጋን ፈሪሓ-እግዚአብሔር ያለው ትውልድ ማትረፍ ይሻለናል።
3) ሥርዐተ ትምህርቶች “በተሟላ የጾታ ትምህርት” እንዲቀረጹ ማድረግ - Compressive Sex Education
በስምምነቱ መሠረት ባለደርሻ አካል አገራት፣ የጾታ ማንነትን፣ የወሲብ ጤንትንና ውልጃን አስመልክቶ፣ ነጻና ሙሉ የሆነ የጤና አገልግሎት እንዲኖራቸው፤ አንዲሁም በተመሳሳይ ጕዳዮች ላይ የዩኔስኮን “የተሟላ የጾታ ትምህርት መመሪያ” ተግባራዊ እንዲከተሉ ይጠይቃል። (አንቀጽ 40፤ ቍ. 6) አገራት ይህን የምዕራቡን ዓለም “የጾታ” ትምህርት የሥርዐተ ትምህርታቸው አካል እንዲያደርጉ ኅብረቱ እርዳታ ያደርጋል። ይህ ብዙ አስከፊ እንድምታ አለው። የዩኔስኮ ትምህርት ራሱ የተቀረጸው የምዕራቡን ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም ታስቢ በማድረገ ነው። ለአብነት ያህል አንድ ማስረጃ ብቻ ልጥቀስ፦
“ወሲባዊ ማንነት ማኅበራዊ ውቅር ነው። ውስብስብ፣ በወቅትና በሁኔታ ተለዋዋጭ ሲሆን፣ በግለሰቦች ልምምድ፣ ሃይማኖታዊ፣ በባህላዊና ማኅበራዊ እሴች ይወሰናል . . .በዚህ ረገድ ልጆች በተለያየ የሕይወት ደረጃቸው ጤናማና ኀላፊነት ያለው ውሳኔ እንዲወስኑ ትምህርት እጅግ አስፈላጊ ነው . . . ‘የተሟላ የጾታ ትምህርት’ (CSE) ዓላማ፣ ልጆች በየትኛውም መንገድ ደስታና ርካታ የሚሰጣቸውን ‘ጤናማ’ የወሲብ ልምምድ ‘ነጻነታቸውን ‘በአገባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ዕውቀት መስጥት ነው።”(International Technical Guidance on Sexuality Education (ITGSE, Conceptual Framework for Sexuality in the Context of Comprehensive Sexuality Education (CSE)፡ The Global Education 2030 Agenda፣ p.17-18, UNESCO, 2018).
ይኸው የዩኔስኮ መመሪያ ልጆችን በዕድሜ ከ 5-8፤ ከ 9-12፤ ከ13-15 እንዲሁም ከ 15ዓመት በላይ በመከፋፈል የምዕራቡን ዓለም የጾታ ትምህርት በርዝር ያቀርባል። ልጆች ከአምስት ዓመታቸው ጀምሮ “ጾታ ማኅበራዊ ውቅር” እንጂ በተፈጥሮ (ባዮሎጂ) የተወሰነ ያለመሆኑን እንዲማሩ ይደረጋል። ከ12 ዓመት በላይ የሆኑት ደግሞ የጾታ ዝንባሌና አገላለጽን (gender identity/norms/expressions) ማስተናገድ፣ የጾታ ዝውውር፣ እርግዝናን የመከላከያ መንገዶች፣ ደስታ እሰከተገኘበትና ‘ጤናማ’ እስከሆነ ድረስ በየትኛውም መንገድ የግል የወሲብ ፍላጐት የማረካት ነጻነት እንዲሁም የሴት ልጅ የውርጃ መብትን በተመለከተ ይማራሉ። (ITGSE, The Global Education 2030 Agenda , “The Social Construction of Gender and Gender Norms”, 50-72).
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ካውንስል በ June 30, 2016 ባሳለፈው ውሳኔ (A/HRC/RES/32/2) መሠረት መንግሥታቱን የሚያማከር የሙሉ ጊዜ “የወሲብ ዝንባሌና የጾታ” አጀንዳ (Sexual Orientation and Gender Identity - SOGI) አማካሪ አለው። በተመሳሳይ መልኩ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች (UN-Women) ዓለም ዐቀፍ የጾታ እኩልነት አጀንዳ ተፈጻሚነት እንዲኖረው የሙሉ ጊዜ አማካሪ (“Dedicated LGBTIQ+ Rights Specialist) አለው። የመንግሥታቱ ሴቶች ቢሮ ባወጣው መመሪያ መሠረት “በተለምዶ ጾታን ‘በወንድነትና በሴትነት’ በመክፈል የሚበይነው ዕይታ አባዊ (patriarchal) እና ወግ ተከተል (heteronormative) በመሆኑ መጋፈጥ ያስፈልጋል” ሲል ይሞግታል። በዚሁ መሠረት “ተፈጥሮአዊ ጾታ (biological sex) የሚለው አሰያየም፣ የጾታ ለውጥ ያደረጉ ሰዎችን ለጾታዊ ኢፍትሐዊነት፣ አድሎአዊነትና አግላይነት አሳልፎ ስለሚሰጥ የእነርሱን “የጾታ ማንነት” የሚያካትትና ዐቃፊ የሆነ ሌላ ተጨማሪ የመገለጫ ስያሜ ያስፈልጋል” የሚል መመሪያ አለው። (LGBTIQ+ Equality and Rights Internal Resource Guide, UN Women, 2022).
4) የቃላት ዐውዳዊ አረዳድ ልዩነትና የስምምነቱ አሳሪነት
በሚከተሉት መረዳቶች ላይ፣ ሙሉ ለሙሉ በሚያሰብል ሁኔት፣ የኢትዮጵያ (በእኔ ግምት የአብላጫው የባለ ድርሻ አካል አገራትን ጨምሮ)፣ ከምዕራቡ ዓለም መረዳት ጋር ተቃራኒ ነው። ይህ ስውር ደባ ነው። ዋና ዋናዎቹን ላንሳ፦
• Gender (ጾታ) – 61 ጊዜ የተጠቀሰ
• Gender equality (የጾታ እኩልነት) – 28 ጊዜ የተጠቀሰ
• Inclusive/inclusiveness (አካታች/አካታችነት) –103 ጊዜ የተጠቀሰ
• Sex/Sexual (ወሲብ./ወሲባዊነት) - 33 ጊዜ የተጠቀሰ
• Universal health coverage / access to reproductive health – (ሁሉን ዐቀፍ የጤና ሽፋን) - በአንቀጽ 29 “ጤና” የሚለው ክፍል የተካተተና ለውርጃ፣ ላልተገደበ ወሲብ፣ ለጾታ ዝውውርና ተያያዥ ቀውሶች በር ከፋች ውል።
• Hate speech/ discrimination/ advocacy of hatred/ discriminatory practices (የጥላቻ ንግግች፣ አግላይ ተሟጋችነት) - 45 ጊዜ የተጠቀሰ ሀሳብ - ለወንጌል መልእክት፣ በተለይም የክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነት መናገር፤ የጋብቻን ክቡርነት፤ ጾታና ወሲብ፤ ውርጃና ተመሳሳይ መጸሐፍ ቅዱሳዊ ዕይታዎችን ማስተማር እንደ “ወንጀል” የሚታይ ያደርጋል። በእነዚህ መሠረታዊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ላይ በምዕራቡ ዓለም ያለቸው ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ፈተና ውስጥ እንዳለች ልብ ልንል ይገባል።
የዚህ ስምምነት ሕጋዊ አሳሪነት የባልደርሻ አገራትን ሉዓላዊነት የሚሸረሽር ነው። እጅግ አሳሳቢው አገራት ስምምነቱን በዓለም ዐቀፍ መድረኮች የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸው ስምምነት መደረጉ ነው (አንቀጽ 6፤ ቍ. 3፤ አንቀጽ 88፤ ቍ. 5)። ልብ እንበል፤ ይህ ስምምነት 27 የአውሮፓ አንዲሁም 79 የአፍሪካ፣ የካሪቢይ እና የፓሲፊክ፣ በድምሩ 106 አገራት በሥራቸው ያለውን ወደ ሁለት ቢሊዪን ሕዝብ የሚወክል ነው። ይህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካለው ወንበር ከግማሽ በላይ ማለት ነው። በስምምነቱ ላይ የተዘረዘሩት ጕዳዮች ሁሉ ባለድርሻ አካላት፣ በአገር፣ በአኀጉርና በዓለም ዐቀፍና መድረኮች (ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታታት) ላይ የማስፈጸም (adoption of common positions on the world stage) ግዴታ ይኖራቸዋል። በዝምታ የድምፅ ተዐቅቦ ወይም በተቃውሞ ረድፍ መቆም አይቻልም። (አንቀጽ 1፣ “ዓላማ”)።
5) ማኅበራዊ መገናኛዎች ዐቃፊ፣ አካታችና “ጾታ ደጋፊ” እንዲሆኑ የሚዲያ ፓሊሲዎችን ማስረጽ - Gender Mainstreaming
በተደጋጋሚ የሚነገር “እንግዳ ዐሳብ” እያደር ተቀባይነት እንዲሚኖረው እናውቃለን። የምዕራቡ ዓለም ባህል ምን ያህል በትውልዳችን ላይ ተጽእኖ እንዳለው የምንገነዘበው ሐቅ ነው። እውነትና ግብረገባዊነት አንጻራዊ የሆኑበት፤ እንዲሁም፣ ሁሉ ዐቃፊነትና አካታችንነት የሰለጠኑበት ዘመን ነው። ይህ ስምምንት “መቻቻልና መቀበበል፣ አካታችና ዐቃፊ” በሚሉ እስቤዎች፣ የማኅብረሰብን ሃይማኖታዊ እሴቶች፣ ባህልና ወግ ይሸረሽራል። አንዱ ዋናው መንገድ የምዕራቡን ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም በሚዲያ፣ በማኅበራዊና በፓለቲካዊ ፓሊስዎች ውስጥ ማስረጽ ነው። (አንቀጽ፤ 2፣ ቍ. 5)።
ምክር - ከብዙ ትሕትና ጋር
ይህ ስምምነት ብዙ ጠቃሚ ትብብሮችን ይዟል። ሆኖም ለከፋ ችግር የሚያዘጋጀን ዕቅድ እንዳለውም ልብ ልንል ይገባል። ብዙ ጥበብና ማስተዋል የሚጠይቅ እርማት ያስፈልገዋል። የምዕራቡ ዓለም “የሰው ልማትና ዕድገት” እሳቤ እግዚአብሔር የለሽና ሰውን የራሱ አምላክ ያደረገ ዓለማዊነት (Secular Humanism) ነው። እውነተኛ “የሰው ልማት” ፈሪሓ- እግዚአብሔርን እንዲሁም የሰውን አምሳለ መለኮት ተሸካሚነት ያማከለ ነው። እናስተውል፣ በጥቂቶች በተያዘው የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ ብልጽግና አብላጫውን የዓለም ሕዝብ ጨቍኖ ያያዘና ኢፍትሐዊ ነው። በምዕራቡና በቀረው የድኾች ዓለም መካከለ ልክ እንደ የሰማይና የምድር የርቀት ከፍታ ያህል ያለው የሀብት ክፍፍል ልዩነት ይህን ሐቅ ያመለክታል።
ለቤተ ክርስቲያን - ይህን ስምምነት የሚያጠናና ነገረ መለኮታዊ እንድምታዎቹን የሚያሳየን የባለሙያዎች ስብስብ በመፍጠር ሕዝብን ማንቃት እንዲሁም መንግሥትን መመከር ያስፈልጋል። ትልቅ አደጋ በፊታችን አለና! በብዙ ሞራል ዝቅጠት ውስጥ በተዘፈቀ፣ አምላክ የለሽ፣ እውነት አንጻራዊ ሆኖ በደበዘዘበት የምዕራቡ ዓለም ባህል ተጽእኖ ሥር ለሚያድጉ ልጆቻቻንንና ለመጨው ትውልድ ልናስብ ይገባናል። በእርዳታና በሰብአዊ መብት ሽፋን በአገራችን ላይ ያኮበኮበውን የምዕራቡን ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም አጀንዳ በቸልተኝነት ብንሳልፍ መዘዙ የከፋ ነው የሚሆነው። በዘረኝነት፣ በክፍፍል፣ በሐሰት አስተምህሮና በዓለማዊነት እንቅርት ላይ፣ ልጆቻችንን ሊበላ ያኮበኮበው የሞራልና የወሲብ ልቅነት አውሬ ተጨምሮበት ምን ይተርፈናል? ቤተ ክርስቲያን ስትወደቅ ትውልድም አብሮ ይወድቃል። ወደ ወንጌል እንመለሰ፤ ለትውልዱም ብርሃንና ጨው እንሁን!
ለቤተ ሰብ - እንንቃ፤ እንጸልይ! በጋብቻ፣ በጾታ ማንነትና በቤተ ሰብ እሴቶቻችን ላይ ግልፅ ጦርነት ታውጇል። ልጆቻችንን በቃልና በሕይወት ምስክርነት እናስተምር። እኛ ካላስተማርናቸው፣ ክፉው ባህል ያስተምራቸዋል። ልጆቻችንን ቄሳር ሳይሆን፣ እኛ ነን ልናሳድግ የሚገባው። እንደምናስተውለው፣ በምዕራቡ ዓለም ነውር የሆነው በአደባባይ በሕጋዊ ፈቃድ ይከበራል፣ ክብር የሆነው "እንደ ነውር" በሕግ ተከልክሎ ይሰደዳል። ነግ በእኛ ነው፤ እናሰብ፤ በቤታችን ክርስቶስና ቃሉ ይሰልጥኑ!
ለመንግሥት - በዚህ ስምምነት አንቀጽ 99 መሠረት እርማት መጠየቅ ይቻላል። በስምምነቱ በተነሱት ስድስት ዐብይት ርእሰ ጕዳዮች ለአገራችን ያላቸው ፋይዳ በባለሙያዎች የሰከነ ጥናት የተደረገ ይመስለኛል። ሆኖም በዚህ አነስተኛ ጽሑፍ ላይ እንዳነሳሁት ጾታን፣ ወሲብን፣ ውርጃን፣ ሰብአዊ መብትንና የጾታ ጤና ትምህርትን አስመልክቶ የአገሪቱ አረዳዳ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። የስምምነቱ አንዱ ትልቁ ችግር ቃላት ዐውዳዊ አፈታት እንዳላቸው ግምት ውስጥ ያለማስገባቱ፤ ወይም ሆነ ብሎ መተው ነው። የአገራችንን አረዳድ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። ሰላም፣ ፍትሕና የአገር ብልጽግና አይለያዩም። በፍትሕ፣ በሰላም፣ በይቅር ባይነት፣ በዕርቅና በፈውስ ላይ ወደ ተመሠረተ አገራዊ መግባባት መሄድ ይገባናል። የዐመፅ ዑደት የመሰበሪያው መንገድ ይኸው ብቻ ነው። የድኽነት ቀንበራችንን ይበልጥ ካከበደው ዐመፅ-መር የፓለቲካዊ አዙሪት መውጣት አለብን። በእርዳታ የበለጸገ አገር የለም፤ በሰላም ዋስትና፣ በፍትሕ መስፈን፣ በሕግ የበላይነት መሰልጠንና በሥራ ትጋት እንጂ። በአንድ ጊዜ እርዳታ ፈላጊና የእርዳታውን ውል ተደራዳሪ ልንሆን አንችልም።
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ያድስ፤ አገራችንን ይባርክ፤ ይጠብቅም!
አሜን!