አልጠፋ ያለ እሳት ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍና ለቀሪዎች አባቶቻችን የሚያስተላልፈው መልዕከት፡፡

መጽሐፍ አልጠፋ ያለ እሳት (የአገልግሎቴና የኢትዮጵያ ካሪዝማዊ እንቅስቃሴ አጀማመር ትዝታ )
ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍና ለቀሪዎች አባቶቻችን የሚያስተላልፈው መልዕከት፡፡ በዮሐንስ ተፈራ
ደራሲ ፓስተር /ዶ/ር አሰፋ ዓለሙ መስክረም 2017
የገጽ ብዛት 394
አሳታሚ ሙሉ ወልደ ማርያም
አርታዒ ታምራት ሥመኝ ረታ
የሚገርም የኢትዮጵያን የጴንጤቆስጤያዊ አብያተክርስቲያናት ታሪክና አጀማመር አስመልከቶ እኔነት ሳይጨመርበት የተጻፈ መጽሐፍ ብል ያገነንኩ አይመስለኝም፡፡ በተለያዩ ወከባዎች ውስጥ ሆኘ ቀደም ብዬ ላነበው ሲገባ ብዘገይም እንዳያልቅብኝ እየተጨነቅሁ ( ያነነበብኩት ከሰው ተውሸ ቢሆንም የኔ መንገድ ላይ ነው) አንብቤ የጨረስኩት መጽሐፍ ነው፡፡ ደራሲውን በአካል የማግኘት ዕድል ባይገጥመኝም ዝናቸውን ከብዙ ሰዎች ሰምቼ ነበር፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ወደጌታ ሊሄዱ ሁለት ወራት አካባቢ ሲቀራቸው ከቦኩም ጀርመን ከወንድም ተወልደ ዮሐንስ ባለቤት ከእትዬ ገነት ጋር ሆነን እሳቸውንና ወንድማቸውን ደበበ ዓለሙን በስልክ አነጋግረናቸው ስለወንድም ተወልደ ዮሐንስ ሕይወት ምስክርነታቸውን ሰጥተውኝ ነበር፡፡ በመጽሐፋቸውም ላይ ዛሬ በአባቱ ዕቅፍ ያለውን የጀርመኑን ጋሽ ተወልደ ዮሐንስን ደጋግመው አንስተውታል፡፡
ይህን መጽሐፍ ሳነብ ስለ ፓስተር ዶ/ር አሰፋ አለሙ ከሰማሁት ይበልጥ እንዳውቅና በብዙ መልክ ከሌሎች የሰማሁትን “ ከፈረሱ አፍ” እንዲሉ በባለታሪኩ በራሳቸው በዚህ መልክ ተጽፎ የማንበብ ዕድል ስለተፈጠረ እጅግ እድለኛ ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌሎቻችንም ይህን መጽሐፍ ያላነበብነው ሁሉ አግኝተን እንድናነበው አበረታታለሁ፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት መጻሕፍትን በተመለከተ በአገራችን ትልቁ ችግር መጽሐፍ መጻፍ የሚገባቸው አለመጻፋቸው ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታቸው ዘመናትን ያስቆጠሩ፣ ቢጽፉ ኖሮ የኖሩት የግል ሕይወታቸው የእውቀት ክምችታቸው፣ ያሳለፉት የኑሮ ውጣ ውረድና የአገልግሎት ስኬትና ተግዳሮት ተደምሮ ለአሁኑም ሆነ ለመጪውም ትውልድ ታላቅ ትምሕርት ሊሰጡ ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን መጻፍ የሚገባቸው አባቶችና እናቶች ታሪካቸውን ስላልጻፉት ለማንበብና ለማወቅ አልታደልንም፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልገባኝ ሁኔታ እንዲጽፉ እየተለመኑ፣ ቴክኒካል ዕርዳታም ካስፈለገ ለመስጠት እየተጠየቁና ቃል እየተገባላቸው ሊጽፉ ፈቃደኛ ባለመሆን ታሪካቸውን ብቻ ሳይሆን የጋራ ታሪካችንን አግዚአብሔር ባስቀመጣቸው ታሪካዊ ዘመን ውስጥ ያለፉበት ሁሉ የግላቸው ሳይሆን የቤተክርስቲያንመሆኑን አልተገነዘቡትም ፡፡ በመቀጠልም የነሱ ታሪክና የሕይወት ተሞክሮና ግለ ታሪከ የነሱን ፈለግ የምንከተል ቅዱሳን ሁሉ ንብረትና ሃብት መሆኑን ባለመገንዘብ ሳያስረክቡን ፣ ሳይነግሩን፣ ቅርስ ሳያስቀምጡልን ይዘውት ሊሄዱ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅስ ማለፍ የማልፈልገውና እንደምሳሌ ሊያገለግል የሚችል ነገር አለ፡፡ ፓስተር ገነቱ ይግዛው የሚባሉ ቺካጎ የነበሩ መጋቢ በየአመቱ አትላንታ ጆርጂያ በሚደረገው የፓስተሮች ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ቢያንስ ለ 3 ተከታታይ ዓመታት አግኝቻቸው ነበር፡፡ ፓስተር ገነቱ ጋር በሻይ ዕረፍትና ከዚያም ረዘም ባለው የምሳ ዕረፍት ላይ ጠጋ እያልኩ አንዳንድ የውይይት ርእስ እያነሳሁ ሳናግራቸው ከአፋቸው የሚወጣው ሁሉ ለትውልድ መተላለፍ የነበረበት ታሪክ ነበር፡፡ ይህ የሚነግሩኝ ነገር ሁሉ ተመዝግቦ ለትውልድ መተላለፍ ያለበት ታሪክ ነውና እባክዎ መጽሐፍ ይጻፉ ብዬ ተማጽኛቸው እሳቸውም እያሰቡበት አንደሆነ ገልጸውልኝ ነበር፡፡ ፓስተር ገነቱ ዛሬ በአባታቸው ዕቅፍ ውስጥ ናቸው ፡፡ መጽሐፉን ጽፈውትም ይሁን የተዘጋጀና ያልጨረሱት ነገርም ቤተሰቦቻቸው ጋር ካለ ለመጨረስና ለንባብ ለማብቃት ልንረባረብበት የሚገባ ነገር ይኖር እንደሆነ የማውቀው የለም፡፡ ለምሳሌ ፓስተር ገነቱ ካጫወቱኝ ነገር አንዱ የሚከተለው ነበር፡፡ ዶሎስና (DOULOS Hope) ሎጎስ (Logos Hope) በሚባሉ በመላው ዓለም ወደቦች እየተዘዋወሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለተገልጋዩ ሕብረተሰብ በጣም ዝቅ ባለ ተመጣጣኝ ዋጋ የሚያሰራጭ የመጻሕፍት ኤግዚቪሽን ያካሂዱ ነበር፡፡ ከነዚህ መርከቦች አንዷ DOULOS የተባለችው መርከብ ወደ ኢትዮጵያ ወደቦች አንድትሄድ (በዚያን ጊዜ አሰብና ምጽዋ የኢትዮጵያ ወደቦች ነበሩ) በመወሰን የሚሽኑ አስተዳደር ኢትዮጵያን በጉብኝት ፕሮግራሙ ያስገባል፡፡ ከዚያም DOULOS መርከብ ወደ ኢትዮጵያ ተልካ ምጽዋ ትደርሳለች፡፡ ( በነገራችን ላይ DOULOS / ዶሎስ በግሪክ ባሪያ ፣ አገልጋይ ማለት ነው) አስተናጋጆቹ በዚያን ጊዜ የምጽዋ ወደብ ከአዲስ አበባ በጣም የራቀ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አላስገቡም ነበር፡፡ በምጽዋ የሕዝብ ብዛትና የክርስቲያን መጻሕፍት ያውም በእንግሊዝኛ ለማሰራጨት ምጽዋ ያን ያህል ብቁ ከተማ አልነበረችም፡፡ የዚህን ስራ ቅንጅት ደግሞ በኢትዮጵያ ወገን ከሚከታተሉት አንዱ ፓስተር ገነቱ ነበሩ፡፡ ምን ይሻላል? መርከቧ ኢትዮጵያ ድረስ መጥታ የተፈለገውን ያህል ግልጋሎት ሳትሰጥ ኢትዮጵያ እንዲሰራጭ የሚፈለገውም መጽሐፍ ሳይሰራጭ መቅረቱና ተልዕኮው የተፈለገውን ያህል ሊሳካ አለመቻሉ ያሳዝናቸዋል፡፡ የኢትዮጵያው አስተናጋጅ ኮሚቴ አባላት ሌላ አንድ አማራጭ ያመጣሉ፡፡ ቢያንስ ሁሉንም መጻሕፍት ማምጣት ባይቻልም የተወሰኑ መጻሐፍት በጭነት መኪና ከምጽዋ አዲስ አበባ መጥቶ የመጻሕፍት ኤግዚቢሽን እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ ታዲያ ኤግዚቢሽኑ የት ይሁን? ሲባል አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተባለ፡፡
ፓስተር ገነቱ የአዲስ አበባን ከንቲባውን ለማናገር ተወክለው ከንቲባው ጋር በቀጠሮ ይገባሉ፡፡ ክቡር ከንቲባው ፓስተር ገነቱን በጥሩ ልብ ተቀብለው ካስተናገዷቸው በኋላ ኤግዚቢሽኑ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እንዲደረግ ፈቀዱላቸው፡፡ ፡፡ ፓስተር ገነቱ ንግግራቸውን በመቀጠል “ ከዚያም የሄድኩበትን ጉዳይ ጨርሼ አመስግኘ ልወጣ ስል ክቡር ከንቲባው “ በነገራችን ላይ ግርማዊ ጃንሆይ እኮ እንደዚህ አይነት ነገር ማድረግ ደስ ይላቸዋል፡፡ ለምን ኤግዚቢሽኑን እሳቸው እንዲከፍቱላችሁ አታደርጉም ?” አሉኝ፡፡ እኔም “ ክቡርነትዎ ይህማ ቢሆንልን እንዴት ደስ ባለን ግን እኛ በምን መንገድ ጃንሆይ ጋር መድረስ እንችላለን? ” አልኳቸው፡፡ ክቡር ከንቲባውም አይ እናንተ ከፈለጋችሁ እኔ ልጠይቅላችሁ እችላለሁ ብለው ጃንሆይን ጠየቁልን፡፡ ጃንሆይም ፈቃደኛ በመሆናቸው ያ የቅዱሳት መጻሕፍት ኤግዚቢሽን ተመርቆ የተከፈተው በግርማዊ ጃንሆይ ነበር “ ብለው አጫውተውኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህን ፓስተር ገነቱ ይግዛው ያጫወቱኝን ጨዋታ ለጋሽ ጋይም ክብር አብ ሳጫውተው እየሳቀ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው ? “ በዚያ የመጽሐፍ ኤግዚቢሽን ላይ የተሰራሁትን ልንገርህ” አለኝ ፡፡ “ እኔም መስማቴን ቀጠልኩ፡፡ “ የባለቤቴ አጥናፍ የነርስ የወር ደመወዝ 113 ብር ነበር፡፡ 100 ብር ሰጥታ መርካቶ ሄጄ የሚያስፈልገንን የቤት አስቤዛ ሁሉ እንድገዛ ላከችኝ፡፡ እኔም ወደ መርካቶ ለመሄድ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በኩል ሳልፍ ረጅም ሰልፍ አየሁ፡፡ ምንድን ነው ? ብዬ ጠጋ ስል የመጽሐፍ ኤግዚቢሽን ነው፡፡ ያውም የክርስቲያናዊ መጻሕፍት ኤግዚቢሽን ፡፡ ከዚያን በፊት ስለ መጻሕፍት ኤግዚቢሽን ከመስማት ያለፈ እንደዚህ ዓይነት ነገር ሆኖ አይቼ አላውቅም፡፡ ሰልፉ መሃል ገባሁ፣ በተራዬ ኤግዚቢሽኑ ውስጥ ስገባ ዐይኔን ማመን አልቻልኩም፡፡ በጭራሽ አገኛቸዋለሁ ብቻ ሳይሆን አያቸዋለሁ እንኳን ብዬ ያላሰብኳቸው መጻሕፍት ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ ብድግ ብድግ እያደረግሁኝ አልፌ ሂሳብ ስከፍል የወር አስቤዛ ግዛ ተብየ ከተሰጠኝ 100 ብር ውስጥ 94 ብሩን መጻሕፍት ገዝቸበት ወደቤቴ መሄዴን አስታውሳለሁ፡፡ አስቤዛ ገዝቶ ይመጣል ብላ ቤት የምትጠብቅህ ሚስትህ መጻሕፍት ተሸክመህላት ስትመጣ የሚሆነውን ነገር እንግዲህ ላንተ አልነግርህም” አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ የጋሽ ጋይምም ስም በ “አልጠፋ ያለ እሳት “ መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህ እንግዲህ የአንድ የጋሽ ጋይም የግል ገጠመኝ ነው፡፡ ሌሎችስ የዘመኑ ወጣቶችና ጎልማሶች በዚህ የዓለም አቀፍ ሚሲዮን አካል በነበረና ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደ ክርስቲያናዊ የመጻሕፍት ኤግዚቪሽን ምን ያስታውሳሉ? ለመሆኑ ግርማዊ ጃንሆይ ማዘጋጃ ቤት ሲደርሱ ማን ተቀበላቸው? ማንስ አበባ አበረከተላቸው? ማንስ ስለኤግዚቢሽኑ ገለጻ ሰጥቶ ኤግዚቪሽኑን እንዲከፍቱ ጋበዛቸው? እሳቸውስ ኤግዚቪሽኑን ሲከፍቱ ምን አሉ? የሌሎች ቤተ እምነቶችስ ስሜት፣ ምላሽና ግንዛቤ ምን ይመስል ነበር? ጋዜጦችስ ምን ብለው ዘገቡት? እዚህ ዝርዝር ውስጥ የገባሁት ገና ብዙ ያልተነገረ ያልተዳሰሰ ታሪክ እንዳለና አሁንም ሊጽፉ የሚገባቸው እንዲጽፉ ፣ በዕድሜ መግፋትም ፣ ከስራ ብዛትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ መጻፍ ካልቻሉ ሊጽፉ በሚችሉ በኩል ሊያጽፉና አስፈላጊ ታሪካችንን (የእነሱ ታሪክ ብቻ ስላልሆነ) ሊተውልን ለሚገባቸው አባቶች በሕግ አምላክ ታሪካችንን ይዛችሁ እንዳትሄዱ ለማለት ነው፡፡በዚህ አጋጣሚ ከአንድ አባት ጋር ስለ መጽሐፍ መጻፍ ስንነጋገር “ ምን መሰለህ ? በእኛ ሕብረተሰብ በተለይ እኛ ባደግንበት ባህል ውስጥ ስለራስ መናገር የሚበረታታ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ስለራሳችን ታሪክ መጻፍ ብዙ አንደፍርም ፡፡ መጻፍ የጀመርነውንም እንኳን ተገቢ ነው አይደለም በማለት መጨረስ አቅቶን ይዘነው እንገኛለን” ብለውኛል፡፡
ወደ ተነሳሁበት ሃሳብ ልመለስና አልጠፋ ያለ እሳት አሁን እዚህ የምንገኝበት ዘመን የደረሰው የኢትዮጵያ የወንጌላውያንና የጴንጠቆስጤያውያን አብያተ ክርሰቲያናትና ክርስቲያኖች እንቅስቃሴ ታሪክ እንዴት ተጀምሮ እዚህ ደረጃ ሊደርስ እንደቻለ በጥቅሉ ያሳያል፡፡ በጥቅሉ ያልኩት ፓስተር አሰፋ የዘመኑ ጨዋነት በሚጠይቀው መስፈርት እኔነት የጌታን ክብር እንዳይሻማ በመፍራት ሰፋ ተደርገው ሊባሉና ሊብራሩ የሚገባቸውን ነገሮች በጥቅሉ እንደተዋቸው መጽሐፉ ያሳብቃልና ነው፡፡ ለምሳሌ በ1964 ዓመተ ምሕረት በሕዳር ወር በታላቁ ቤተመንግስት በንጉሰ ነገሥት ኃይለ ስለሴና በሃያላን ባለሥልጣኖቻቸው ፊት ቀርበው የነበረውን የወቅቱ የጴንጠቆስጤ አምነት አራማጆች ወጣቶችን የቤተመንግስት ውሎ በ4 ገጽ ብቻ አጠቃለው ማለፋቸው ፣ ለአብነት የሚወሰድ ነው፡፡ “እነ አጅሬ” ለደቂቃ በዚያች ሰፈር ቢገኙ ኖሮ ተራራ በሚያክል ፎቷቸው በመሸፈን ስንት መጻሕፍትና ስንት ቪዲዮ ባሰራጩራበት ነበር ብዬ ኃጢአት ውስጥ አልገባም፡፡ ለነገሩ የቀድሞዎቹም በዛ (አንናገርም ጌታ ይክበርበት ) የአሁኖችም ተብዛዛ (ሁሉን ለሜዲያ ፍጆታ) አንደው ጌታ ረድቶን ማዕከላዊ የሆነና የተመጣጠነ ነገር ቢኖር መልካም ነው፡፡ ይሁንና መጽሐፉ የነ ጋሼ አሰፋ ትውልድ በምን አይነት መሰጠትና ክርስቲያናዊ ዲሲፒሊን ራሳቸውን ገዝተው፣ ለዓለም ቅራቅንቦ ሳይሸነፉ ፣ መልካሙን ገድል በመጋደል የከፈሉት ዋጋ ቀላል እንዳልነበረም ያመላክታል፡፡
አልጠፋ ያለ እሳት ዛሬ ስማቸው የተረሳ መረሳትም ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ወደጌታ የመጣን ስማቸውን በጪራሽ ሰምተነው የማናውቀው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገራት ዞረው ወንጌልን ያስፋፉ ቅዱሳንም ስም ተጠቅሶበታል፡፡ አልጠፋ ያለ እሳት መጽሐፍ ሳይሆን በትክክል ፈሩን ሳይለቁ ያሳለፉትን ሕይወት ለትውልድና ለታሪክ አስተላለፈው ማለፍ ላለባቸው የአምነት አባቶቻችን መነሻ (ማውጫ) ሆኖ ፓስተር አሰፋ ሳያስፋፉት ወይም ቀጣዩን ለመጻፍ ዕድል ባለማግኘታቸው የተውትን ክፍተት በመሙላት የበርካታ ድርሳናትና ገድላት መነሻና መንደረደሪያ ሆኖ ሊጠቅም የሚችል ማውጫ (Manual) እንጂ አንድ መጽሐፍ ብቻ አይደለም ባይ ነኝ፡፡በመጽሐፉ ላይ ታሪኩ የተገለጸው ጃንሆይ ! ጃንሆይ ! ጃንሆይ ! ብሎ በመጮህ “ ከእሳት ቃጠሎ የተረፉ 2 ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማስጃ ይዞ ንጉሱ በሚያልፉበት መንገድ ላይ የተኛው የወቅቱ ወጣት መኩሪያ ሙሉጌታ (የዛሬው ጋሽ መኩሪያ) የሚገርም ነው ፡፡ መኩሪያ ከንጉሱ ጋር ያደረገው አጪር ንግግርና ከዚያም በቤተመንግስት ቀጠሮ ተይዞለት ጓደኞቹን ይዞ በንጉሱ ፊት የቀረበበት ሂደት እጅግ ታሪካዊ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በጃንሆይ ፊት ቤተመንግስት መቅረብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተብራርቶ ቢጻፍ ብዙ ቅጾች የሚወጣው የድርሰት ምንጭ የመሆን አቅሙ ከፍተኛ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ ( ሃብትና ስልጣን ቢኖረኝ ለዘመናት ለዕምነት ነጻነት መከበር እያነቡና መስዋዕትነት እየከፈሉ ያለፉትን ሁሉ ለመዘከር ልክ ጋሽ መኩሪያ ጃንሆይ ! ጃንሆይ ! ጃንሆይ ! እያለ ሲጮህ በሚመስል መልኩ አንድ የመታሰቢያ ሐውልት በአዲስ አበባ አንዱ ትልቅ ቤተክርስቲያን በር ላይ አቆም ነበር ፡፡ ያን የሚያይ ሁሉ ምንድን ነው ብሎ ሲጠይቅ “አባቶቻችን እዚህ ዛሬ የተገኘው የአምልኮ ነጻነት ላይ ከመድረሳችን በፊት በዕንባና በጽኑ የእምነት ተጋድሎ አስፋልት ላይ በመተኛት ንጉሱን በመማጸን ጭምር ሞክረው የከፈሉትን መስዋዕትነት እንዲያውቅ ነገር ግን እግዚአብሔር በራሱ ጊዜና ሰዓት ጣልቃ ገብቶ ዛሬ እንዲህ በነጻነት ማምለክ መቻሉ ዘም ብሎ የተገኘ እንዳልሆነ በመገንዘብ እንዳይቀልበት ሊገነዘብ ያስቸለዋል ብዬ ስለማምን ነው፡፡
በጴንጠቆስጣውያን ላይ የደረሰውን መከራና ስደትን በተመለከተ ጋሽ አሰፋ በቅርብ የደረሱበትን ፣ በቅርብ ርቀት ያዩትን እንጂ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ስለነበረው ብዙ አለማለታቸው አንድም ቀጣይ መጽሐፍ እያዘጋጁ ሞት እንደቀደማቸው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል ፡፡ አለበለዚያም ደግሞ ሁሉንም የአገሪቱን እንቅስቃሴ ዘገባ ከአንድ ሰው መጠበቅ የማይገባና ሌሎችም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ የሚያስተላልፍ ይመስለኛል፡፡ለምሳሌ በደሴ ከተማ ኗሪ የነበሩት አቶ ደምሴ አሰሌና አቶ ማርታ የተባሉ የአንደኛ ደረጃ የመንግስት ትምሕርት ቤቶች መምሕራን “ጴንጠቆስጤ” በመሆናቸው ብቻ ከከተማዋ በ24 ሰዓት ካልወጡ የደሴ ከተማ 74 ዕድሮች ሕዝቡ በአንድነት ወጥቶ ሊገድላቸው ተማምሏል ብለው ለመንግስት አሳወቁ፡፡ መንግስትም የሰዎቹን ሕይወት ለማዳን ባዘጋጀው የፖሊስ የጭነት መኪና ዕቃቸው እየተወረወረ በተወሰኑ ሰዓታት ቤታቸውን ለቀው ሕይወታቸው ላይ አደጋ እንዳይደርስ በፖሊስ ታጅበው የሰሩትን ቤት ጥለው ሕይወታቸውን ለማዳን ሲባል ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወሩ መደረጉን በጣም ሕጻን ልጅ ሆኜ ቤታችን ከቤታቸው ከ 200 ሜትር በማይበልጥ ርቀት ስለነበር ሁኔታውን ቆሜ በዐይኔ አይቻለሁ፡፡
አጠቃላይ የዚህች መልዕክቴ አላማ መጽሐፉን ማለትም አልጠፋ ያለ እሳት ለመገምገም ሆነ ለመተቸት ወይም ለማብራራት ሳይሆን ለማንበብ እድል በማግኘቴ የተሰማኝን ስሜት ለማጋራትና ሌሎችም መጻፍ የሚገባቸው እንዲጽፉ ለመማጸን ብቻ ነው፡፡ በ አልጠፋ ያለ እሳት ውስጥ በግልጽ ያየሁት የአማኞች መሰጠት ፣ ለአላማቸው ቆራጥ መሆን ራሳቸውን ከገንዘብና ከዝና ፍቅር መግታትን ነው፡፡ በዚሁም አንጻር የሕዝባችን የብሔራዊና ግላዊ ኩራት ፣ የጨዋነትና የዓላማ ሰውነት መጠን በአገራዊ ፣ ማሕበራዊ ዘርፎች ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ዘርፍም ምን ያህል ወደኋላ እየሄደ መሆኑን በዚህ መጽሐፍ በግልጽ ይታያል፡፡ እነፓስተር አሰፋ አለሙ የከፈሉትም መስዋዕትነት፣ ጠመዝማዛና አስቸጋሪ መንገድ አልፈው በሚያንጸባርቅ የሕይወት ምስክርነት ያስረከቡን ቤተክርስቲያን የአገልጋይነት ደረጃ አሁን ከሚገኝበት ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ቁሳዊ (ንብረት ተኮር) የታይታ (ለሜዲያ ፍጆታ ) ላይ ያጋደለ መሆኑን ስናይ በሰቆቃዎ ኤርምያስ 5፥21 አንደተጻፈው “ አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ” ከማለት ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም፡፡ በመጨረሻም አልጠፋ ያለ እሳት የቤተክርስቲያን ጉዳይ ግድ ይለኛል የሚል ሁሉ ሊያውቀው የሚገባውን ሁሉ ይዛለችና እንድታነቡት አበረታታለሁ፡፡
ማሳሰቢያ
ዶሎስና (DOULOS Hope) ሎጎስ (Logos Hope) የሚባሉት ንብረትነታቸው የሚሽን ሶሳይቲ የሆኑ 2 መርከቦች ነበሩ፡፡እነዚሀ መርከቦች በመላው ዓለም እየተዘዋወሩ በወደቦች ላይ ሲደርሱ የመጻሕፍት ኤግዚቪሽን በማድረግና መርከቦቻቸውን ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ መጻሕፍትን እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በመሸጥ ለሕዝብ እንዲደርስ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ዶሎስ የተባለችው መርከብ በ108 አገሮች ተዘዋውራ በ 22,219,916 ሰዎች የተጎበኘች ሲሆን 3,749,375 ሰዎች መርከቧ ላይ የተደረገ ፕሮግራምን ተካፍለዋል፡፡ መርከቧን ከጎበኙ መካካል 16,930,297 ሰዎች ከመርከቧ ላይ መጻሕፍትን ገዝተዋል፡፡ በአጠቃላይ መርከቧ በ 108 አገሮች ውስጥ የሚገኙ 601 የተለያዩ ወደቦችን ጎብኝታለች፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ሁሉም የመርከቧ ሰራተኞች በሚሲዮናዊነት ጊዜያቸውን መድበው ለተወሰነ ጊዜ በነጻ የሚያገለግሉ መሆናቸው ነው፡፡