ጦርነት ይብቃን
ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች -(መክብብ 9፥18)

“ካለፈው የማይማሩ፣ ይደግሙት ዘንድ ተፈርዶባቸዋል” — ጆርጅ ሳንታያና
“ሰዎች ቢውድቁ፣ እንደ ገና ከወደቁበት አይነሡምን? ሰው ተሳስቶ ወደ ኋላ ቢሄድ፣ ከስሕተቱ አይመለስምን? ታዲያ፣ ይህ ሕዝብ ለምን ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ይሄዳል? ለምንስ ኢየሩሳሌም ዘወትር ወደ ኋላ ትመለሳለች? ተንኰልን የሙጥኝ ብለው ይዘዋል፤ ሊመለሱም ፈቃደኛ አይደሉም።” (ኤር. 8፥3–5)
እግዚአብሔር የይሁዳን ልበ ደንዳናነትና ያንኑ ያከሰራትን የጥፋት ጐዳና በተደጋጋሚ ለመሄድ መወሰኗን የገለጠበት መንገድ፣ እንደ አገር የእስከ አሁኑን አካሄዳችንን የሚያሳይ ይመስለኛል። ይሁዳ ያለፈው የእሥራኤል ታሪክ ያለመማሯ ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በከፋ መልኩ በመድገሟም አዝኗል። “ከከሓዲዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ጻድቅ ሆና ተገኘች።” (ኤር. 3፥11)። ልክ እንደ እስራኤል፣ የአመራር፣ የመንፈሳዊ፣ የፍትሕና የሞራል ቀውስ፣ ይሁዳንም ለራስ ጥፋት አሳልፎ ሰጥቷታል።
በዚህ ዘመን ያለነው እኛም፣ ከትናንቱ መማር ተስኖናል። “ከታሪክ የማይማሩ፣ ስሕተትን ይደግሙት ዘንድ ተኰንነዋል” የሚለው አባባል እኛ ላይ ደርሷል። ከታሪክ የተማርነው ከታሪክ አለመማራችንን ነው” የተሰኘው ሌላው ሸንቋጭ አባባልም የሚያስተጋባው ይኸን መሰሉን ስንፍናችንን ይመስለኛል። አዎ፥ ከትናንቱ የማይማር ሰው በርግጥም መልሶ እንዲሳሳት ቢፈረድበት እንጂ ሌላ ምን ምክንያት ይኖረዋል? በሚዘገንን መልኩ ታሪክ ራሱን የሚደግመውና የሚደጋግመው ለዚያ ሳይኾን አይቀርም። እኛን የሚተካው ትውልድ ደግሞ፣ ከእኛ ባለመማር የከፋ እንዳያደርግ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱና ምሕረቱ ያስበን። እንደ እውነቱ፣ ለእኛም ለመመለስ ጊዜው አልረፈደም።
እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ላይ ቅኝ አገዛዝን በመቃወም ሲታገሉ የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት “የነጻ አውጪዎች” እንቅስቃሴ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ በምዕራቡ ዓለም ትልቅ ድጋፍ አግኝቶ ነበር። ይህንን የዓለም የፓለቲካ ለውጥ በወቅቱ “የእግዚአብሔር ጣት” በማለት ድጋፍ የሰጡ በርካታ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አባል አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ።
በወቅቱ ልቅ ነገር መለኮትን ያራምዱ የነበሩ መሪዎችም፣ “ድነትን” ከፓለቲካዊና ማኅበራዊ ዐርነት ጋር በማያያዝ፣ ከቅኝ አገዛዝ ዐርነት ለማግኘት ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን መንፈሳዊ አልባሳት ለመስጠት ሙከራ አደርገው ነበር። እንዲያውም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በባንግኮክ-ታይላንድ፣ “ድነት ዛሬ” በሚል መሪ ዐሳብ አካሂዶት የነበረው ስብሰባ በዚህ ዕሳቤ የተቃኘ፣ ኢምፔሪያሊዝምን ያወገዘና ቅኝ አገዛዝን የኰነነበት መርሐ ግብር ነበር። ሲቆይ ግን “ነጻ አውጪዎቹ” አንገት በሚያሰደፋ መልኩ ከቀደሙት ቅኝ ገዢዎች ይልቅ ከፍተው ተገኙ። መንፈቅለ መንግሥትን መደበኛ የፓለቲካ ሽግግር በማድረግ አፍሪካ ላለፉት ስድሳ ዓመታታ ፈተኛ ናት። ኾኖም በየትኛውም መልኩ ቅኝ አገዛዝ ይሻል ነበር እያልሁ አይደለም። በፍጹም! ከታሪክ አልተማርንም፤ የዐመፅና የግፍ ዑደቱ ቀጥሏል ለማለት ያኽል ብቻ ነው።
እኛም ብዙ አልተሻልንም። በታሪካችን ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር የለንም — በደም የተለወሰ እንጂ። “በአሮጌ አቍማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማንም አይጨምርም” የሚለውን ቃል እንለዋለን እንጂ፣ ቀደም ሲል የነበረውን የክፋት መንገድ አሁን በድጋሚ፣ ምናልባት እጅግ በባሰ ደረጃ እየሄድንበት እንገኛለን። ለዚህም ሦስት ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል። አንደኛው፣ የታሪክና የቂም እስረኝነት ለወለደው በቀል ሥልጣናችንን መጠቀማችን ነው። ኹለተኛ ደግሞ፣ አፍቃሬ — ሥልጣንና ጥቅም የወለደው አንባገነንነት ነው። ሦስተኛው፣ በተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል ያለው የሥልጣን ሹክቻ የሚያሰነሣው ዐመፅ ነው። ያለን ልምድ በዐመፅ መተካካት ስለሆነ፣ አንዱ ለሌላውን የሚመለከተው ለህልውናው ሥጋትና ፍርሃት በሆነ መልኩ ነው።
እንደምናስተውለው፣ የዐመፅ የፓለቲካችን ሽግግሮች ሁል ጊዜ አፍርሶ ከወለል የሚጀመሩ ናቸው። በመልካሙ ላይ የምንገነባ፣ ደካማውን የምናሻሽል፣ ከመጥፎው ደግሞ የምንማር አይደለንም። ይልቁንም ላለፈው ትውልድ ኀጢአት፣ ተከታዩን ተጠያቂ እናደርጋለን። መልካም ዝክር ቢኖር እንኳን፣ በሕዝብ ልብ እንዳይኖር መታሰቢያውን እንጠፋለን። በዚህ ሳቢይ እንኳን ለአገር፣ ለዓለምም ሊተርፉ የሚችሉ በርካታ መሪዎችንና ምሑራንን አጥተናል።
አስከፊ ድኽነት ይሳለቅብናል፤ በየባዕድ ምድሩም በስደተኝነት ያንከራትተናል። የሰላም እጦትና የፍትሕ ጩኸት በየምዕራቡ ዓለም አገር መንግሥታት መቀመጫ ደጃፎች ያስጮኸናል። በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ ረገጣ፣ በተደራጀ አገር ዘረፋ እና በአገር ውስጥ ስደተኝነት ደረጃ አስከፊ ከሚባሉት አገሮች ተረታ ከፊተኞች ነን። የብዙ ሺህ ዓመታት አኩሪ የነጻነት ታሪክ አለን። ኾኖም ሰው በዘር (በዘውግ) ማንነቱ ብቻ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቈጥሮ የሚፈናቀልባትና የሚጨፈጨፍባት የብዙ ምፀት ምድር የሆነች አገር ነው ያለችን።
ከትግራይ፣ ከአፋርና ከአማራ የጦር ሜዳ ውሎዎች ማግሥት፣ በአማራ ክልል የተነሣው የጦርነት እሳት፣ እኛም ከፍ ሲል በኤርምያስ ላይ እንደ ተጠቀሰው “ተንኰልን [ያለመተማመንን፣ ቂምን፣ ጥርጥርን፣ ዐመፅን] የሙጥኝ” ብለን መያዛችንን፤ እንዲሁም የሚያስከተለውን ጥፋት እያወቅን ያለመመለሳችን ደግሞ የልባችንን ጥንካሬ ያሳያል።
የማሰብና የመናገር ነጻነት ፋይዳው ብዙ አልተረዳንም፤ ይልቁንም ሌሎችን በቃላት የምንገድልበት መርዝ ኾኖብናል። ይህም ምፀት ነው። ቅዱስ ቃሉ እንደሚል፤ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።” (ምሳሌ 12፥18)። ክብረ-ነክ ንግግር፣ አንቋሻሽነት፣ ንቀትና ሰባሪ ትችት የቂምና የትርክት አዙሪቱን ይበልጥ አክርረውታል እነዚህ ምግባሮች እንደጥልፍ ከብዙ ብሔሮች፣ ቋንቋዎችና ሃይማኖቶች የተጠለፈውን አገራዊ አንድነት ከሥሩ አናግተውታል።
ለውጥና ሰላም ፈልገን፣ አሮጌም አቁማድ ይዘን አይሆንም። ታዲያ ከዚህ ወዴት እንሂድ?

ከመንፈሳዊው ልጀምር። በተደጋጋሚ እንዳልሁት፣ በቤተ እምነቶች፣ በመንግሥት እና ፓርቲዎች መካከል ግልጽ የሆነ የግዛት ድንበር ማበጀት ዋናና አስፈላጊ ነው። በተለይም ለአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ይህን ከትልቅ ትሕትና ጋር በአጽንዖት ለማሳሰብ እወዳለሁ። ለእውነትና ለፍትሕ በመቆም፣ ኀይላትን መገሠጽና መምከር የሚችሉት፣ ከፓለቲካ ተጽእኖ ውጭ በሆኑ መጠን ብቻ ነው። የፍርድ ሚዛን ሲዛነፍ፣ የአስተዳደር በደል ሲደርስ፣ ነጻ የሆነ የሕዝብ ፖለቲካዊ ምርጫ ብያኔ ሲካድ፣ ሕዝብ ለሰላምና ፍትሕ ጩኸቱ ድፍን ጆሮ ሲገጥመው፣ ቤተ ክርስቲያን ለመናገር ዐቅም የሚኖራት በራሷ ግዛት እስከ ኖረች ድረሰ ብቻ ነው። ጤናማ ያልሆነ ቍርኝትና የውለታ እስረኝነት፣ መጠኑ ቢለያይም፣ ልክ እንደ ሌሎች ቤተ እምነቶች፣ እኛንም ጐድቶናል፤ የሞራል ልዕልናም ነሥቶናል። ቆም ብለን በሰከነ ልብ ያለንበትን ዐሳሳቢ ሁኔታ ልብ ልንል ይገባል። ከየትኛውም ጊዜ በላይ ምስባኮቻችንን ከፓለቲካዊ ተጽዕኖዎች የመጠበቅ ዐደራ ወድቆብናል። ይህ እርሾ ከአሁኑ ካልተደፋ ትልቅ አደጋ አለው።

በእውነተኛና በፍሬ በሚገለጥ ንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ። ይህም ማለት የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው “የውደቀታችን ጥልቀት መረዳት፣ መመለስና ወደ ቀናው መንገድ መመለስ” ማለት ነው። “እንግዲህ ከየት እንደ ወደቅህ ዐስብ፤ ንስሓ ገብተህ ቀድሞ ታደርገው የነበረውን ነገር አድርግ” (ራእይ 2፥5) የእግዚአብሔር የምሕረት ደጆች አልተዘጉም። ፈሪሓ እግዚአብሔርን ከረገጥን፣ ምን ተስፋ አለን? ስለዚህ በግልና በጋራ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንድናገኝ በእውነተኛ ንስሓ ወደ እርሱ እንመለስ።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሸንን ሥራ መደገፍ። የተረዳሁትን ያህል ይህ ኮሚሽን “የልብን ጕዳይ” ለመድረስ ጥረት እያደረገ ነው። ፈርጀ ብዙ የመስተጋብር ፈውስ ያስፈልገናል — ከእግዚአብሔርም፤ ከእርስ በእርስም። የታሪክ አረዳድ፣ የአገረ መንገሥት አወቃቀር፣ ሕገ-መንግሥት መሻሻል፣ በፌዴራሊዝምና በክልላዊነት መካከል ሊኖረው ስለሚገባው ሚዛናዊ፣ ጤናማና ተዓማኒነት ያለው ግንኙነት፣ የወሰን ጕድይ፣ ቅቡልነት ያለው የድምፅ ውክልናና ተመሳሳይ ጥያቄች አገራዊ መግባባት ይሻሉ። በፍትሕ፣ በሰላም፣ በይቅር ባይነት፣ በዕርቅና በፈውስ ላይ ወደ ተመሠረተ አገራዊ መግባባት መሄድ ይገባናል። ለሁሉም ቅን ምክክር ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ በዋነኛነት የልብ ፈውስን ይጠይቃል። ብዙ ነውጥ ባለባት አገር ኮሚሽኑ ሥራውን የሚያስተጓጉሉ ብዙ ችግሮች ሊኖር እንደሚችሉ እገምታለሁ። ቅዱስ ቃሉ፣“የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” (ምሳሌ 13፥12) እንደሚል፣ የሕዝብ ልብ እንዳይዘል ሥራውን በፍጥነት መጀመሩና ከመንግሥት፣ ተቃዋሚዎች፣ ከቤተ እምነቶችና ከአገር ሽማግሌዎችና ምሑራ ማኅበረ ሰብ በሙሉ ያልተቆጠበ ትብብር ማግኘቱ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ፓለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን ከዘረኝነት ሊፋቱ ይገባል። “ብሔርተኝነት” የራስን ማንነት ማግዘፍ፣ ሌላውን ማኮሰስ ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን አምሳለ አምላክ ተሸካሚነት መግፈፍ ነው። ሰው ክቡር ነው። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነውና! ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ የትኛውም ግዛት ያለስጋት እንዲኖርና የምድሪቱም በረከት እኩል ተካፋይ እንዲሆን የሚያስችል የእውነተኛ የሰብዓዊነት ተሓድሶ ያስፈልገናል። “እኔነትን” መካከለኛ ያደረጉ የጥላቻ፣ የፍርሃት ያለመተማመንና የአግላይነት ግድግዳዎችን ማፍረስ። የኢትዮጵያዊነት ፋይዳ ልክ ከኅብረ ቀለም እንደ ተሠራ ጥልፍ፣ ከልዩ ልዩ ብሔረሰባዊ መለያዎቻ (ባሕልና ቋንቋ) የተበጀ ጌጥ ነው። በጥምረት ያስተሳሰሩን ትውልድ ተሻጋሪ ፋይዳዎቻችን፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶቻችንን አልፈው መታየት ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ፣ መንግሥትን ጨምሮ ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው መልሰው ወደ ውይይት መመለስ። የዐመፅ ዑድት የመስበሪያው መንገድ ይኸው ብቻ ነው። የእስከአሁኑ አካሄዳችን አድካሚ፣ አክሳሪና መከራ ያጨድንበት ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚል፣ “መንግሥት “ለመልካም ነገር የሕዝብ አገልጋይ” ነው (ሮሜ. 13፥4)። የመንግሥት አወቃቀር፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደር መርሕ፣ ፍትሐዊነትና ተኣማኒነት የሚለካው በዚሁ እውነት ነው። ቅቡልነቱ ሲጐዳና የሕዝብ ልብ ሲሸሸው ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ጦርነት በማቆም፣ ለምክክር፣ ለዕርቅና ለሰላም ጥሪ ማድረግ ይገባዋል። የሰው አምሳለ ተሸካሚነትና ክቡርነት እንዲሁ ሰላም የቤተ እምነቶች ሁሉ የጋራ ዕሴቶች ናቸው። በዚሁ መሠረት፣ የሃይማኖት መሪዎች ለጭፍን ውግንና ወይም ጥላቻ መሣሪያ ከመሆን ይልቅ ለላቀው አምላካዊ ዐደራ በመኖር የዕርቅና የሰላም መንበር በመሆን አገራችንን ለመታደግ ከምንጊዜውም በላይ ወቅቱ አሁን ነው።
እንደ ወንጌላዊ አማኝ የሚከተለውን በመጨመር ዐሳቤን ልደምድም። ቤተ ክርስቲያን የከርስቶስ እንደራሴ ናት። የመንግሥትም ኾነ የተቃዋሚ ፓርቲ አይደለችም። እንደ አማራጭ የክርስቶስ ማኅበረሰብ፣ አማኞች በሙሉ የተሻለውን መንገድ የመኖርና የማሳየት ትልቅ ዐደራ አለብን። የክርስቶስን ሥር-ነቀል የጽድቅ መንገድ በመከተል፣ ጨውና ብርሃን ልንሆን ተጠርተናልና። የወንጌል ዐዋጃችን እውነተኛነት፣ ተዓማኒነትና ቅቡልነት የሚለካው ከክርስቶስ ጋር የሚገጥም ሕይወት በኖርንበት መጠን ነው። ክርስቶስ፣ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ፣ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ. 5፥16) እንዳለ፣ በመስቀል የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ሰዎች በእኛ ውስጥ ማየት መቻል አለባቸው። ሕይወት የጐደለው ምስክርነት ዐቅም የሌለው ከንቱ ልፍለፋ ነው። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷል” ስንል፣ ይህን “ዘርና ማኅበራዊ ድንበር የማያውቅ ንጹሕ መውደድ” ሕዝባችን በእኛ ውስጥ ማግኘት መቻሉ ነው።
እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ አገራችንን በሰላምና በዕርቅ መንገድ ይምራ፤ ከዐመፅ ዑደት ይታደጋት፤ በሰላሙም ይጠብቃት። አሜን!