የእምነት መግለጫ

 

1. መጽሐፍ ቅዱስ፦

በብሉይና በአዲስ ኪዳን ያሉት ስድሳ ስድስቱም መጻሕፍት ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የፃፉት መሆኑን፣

በመጀመሪያው ጽሁፍ ምንም ስህተት የሌለበት፣ የቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ስርዓትና ምንጭ መለኪያ የሆነ

የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ለአማኞችም ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናትና ለመምከር ሙሉ ሃይልና

ስልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ እናምናለን። [1]

2. እግዚአብሔር፦

በሰማይና በምድር የሚገኙትን የሚታዩትንና የማይታዩትን ፍጥረታት ሁሉ በፈጠረ ፍጹም፤ ህያው፤ ሁሉን ቻይ፤

ዘለዓለማዊ፤ የማይወሰን፤ የማይለወጥ፤ ሁሉን አዋቂ፤ ራሱን በማይከፈል ኑባሬ በሶስትነትና በአንድነት ይዞ በሚኖር አብም

ወልድም መንፈስ ቅዱስም በሆነው አንድ አምላክ እናምናለን። [2]

o እግዚአብሔር አብ፦ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁ የሆነዉን ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም ኃጢአት

በመስቀል ሞት መስዋዕት እንዲሆን የሰጠ፤ ልጁን በማመን አዳኝና ጌታ አድርገው ለሚቀበሉት ልጆቹ ይሆኑ

ዘንድ ስልጣን የሚሰጥና ከእርሱ ሰርጾ የሚወጣውን መንፈስ ቅዱስንም በወልድ ስም የላከ እንደሆነ

እናምናለን።[3]

o እግዚአብሔር ወልድ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ የሆነ፤ ከአብና ከመንፈስ

ቅዱስ ጋር ፍጹም የተካከለ መለኮት፤ ከድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሰ፤ ፍጹም ሰው ፍጹም

አምላክ የሆነና ለዓለም ሁሉ ኃጢአት በቀራንዮ መስቀል ተሰቅሎ በመሞት ወደ ሲዖል ከወረደ በኋላ

በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሳና ባፈሰሰው ክቡር ደም ከእግዚአብሔር አብ ጋር ብቸኛ

የመታረቂያ ምክንያት ሆኖ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ በማረግ በአባቱ ቀኝ የተቀመጠ፤ በሰማይ

በዘለዓለማዊ ሊቀ ክህነት አገልግሎት በተሾመ፤ ስለ ኃጢአተኞች በሚማልድና በዓለም መጨረሻም

በሙታንና በህያዋን ላይ ሊፈርድ ባለው፤ ዳግመኛ በሚመለሰው እናምናለን።[4]

o እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፦ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮትነቱ እኩል የሆነ፤

የሥላሌ ሦስተኛ አካል፤ የአብና የወልድ መንፈስ የሆነ፤ የራሱ ስብዕና ያለው፤ የሚፈጥር፤ሀይወትንም

የሚሰጥ፤ በነቢያት አድሮ ትንቢት ያናገረ፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ሲከብር ከአብ ሰርፆ በመውጣት በሐዋርያት

ላይ የወረደ፤ ዓለምን ስለ ኃጢአት ሰለ ጽድቅና ስለ ፍርድ በመውቀስ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ሰዎች

እንዲድኑ የሚረዳ፤ በአማኞች ውስጥ የሚያድር፤ ያመኑትንም የሚያትም፤ የሚመራና ሃይልን የሚሰጥ

እንዲሁም በመቀደስና የፀጋ ስጦታዎችን በማደል በቅዱሳን ህይወት እንደሚሠራ እናምናለን።[5]

ሀ) የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በደህንነት ( በዳግም ልደት)

መንፈስ ቅዱስ የሰውን ልጅ ስለ ኃጢአቱ በመውቀስ በክርስቶስ ኢየሱስ ለነፍሱ የተዘጋጀውን ምህረት

ይነግረዋል፤ ንስሃ ገብቶ በክርስቶስ በማመን ዳግመኛ እንዲወለድና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን ይረዳዋል፤

የልጅነት ማረጋገጫ ማሕተም በማድረግ በክርስቶስ አካል ውስጥ ያስገባዋል፤ ቃሉን በመግለጥ በህይወቱ

የመንፈስ ፍሬ እንዲታይ ያደርጋል። [5 ሀ]

ለ) በመንፈስ ቅዱስና በእሳት መጠመቅ

መጥምቁ ዮሐንስ እንደተናገረው እግዚአብሔር አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል በእምነት ለሚጠባበቁና

ለሚራቡ ዳግም ለተወለዱ ልጆቹ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃል። ዓላማውም

ወንጌልን በድፍረትና በኃይል እንዲመሰክሩ ነው። ጌታ ኢየሱስም ወደ አባቱ ከመሄዱ በፊት ከላይ ኃይል

እስክትለብሱ ከኢየሩሳሌም ከተማ እንዳትወጡ ብሎ አዘዛቸው። ሐዋርያት በዮሐ. 20፥22 መንፈስ ቅዱስን

እንደተቀበሉና ዳግም እንደተወለዱ ግልፅ ነው።

ጌታ በገባው የተስፋ ቃል መሠረት በኢየሩሳሌም በጸሎት እየተጉ በተስፋ ሲጠባበቁ ለነበሩ 120 ቹ አማኞች

ላይ በግልጽ በምልክትና በድንቅ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ተቀብለዋል። አንዱም ምልክት በሌላ ልሳኖች

መናገር ነበር። ይህም የተስፋ ቃል በበዓለ ኃምሳ ቀን ብቻ እንዳልቆመና ባመኑት ህይወት የሚቀጥል እንደሆነ

መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን አማኞች የዚህ ታላቅ የተስፋ ቃል ተካፋዮች

እንዲሆኑ ታስተምራለች፣ ታበረታታለች። [5 ለ]

ሐ) የጸጋ ስጦታዎች

የጸጋ ስጦታዎች ከተፈጥሮ ስጦታዎች የተለዩ ናቸው፥ መንፈስ ቅዱስ እንደ ወደደ ለቤተክርስቲያን የጸጋ

ስጦታዎችን ይሰጣል። በ 1 ቆሮ. 1፥7 “ እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ

” አንዳች የጸጋ ስጦታ እንኩዋን አይጎድልባችሁም ተብሎአል። በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ውስጥ ወደ 18

የሚሆኑ የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች እንዳሉ ተጠቅሰዋል፤ ቤተክርስቲያናችንም እነዚህ የጸጋ

ስጦታዎች በዘመናችንም መንፈስ ቅዱስ እንደፈቀድ በአማኞች ሕይወት ውስጥ እንደሚያፈስና

እንደሚሞላ ታምናለች፣ ታበረታታለች ታስተምራለችም።[5 ሐ]

3. ሰው፦

ሰው በእግዚአብሐ.ር አምሳል ተፈጥሮ በኃጢአት ወድቆ ሙት በመሆን የጠፋ ሲሆን የሰውን ዘር ከኃጢአት ለማዳን

በመስቀል ላይ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ከሙታን በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በማመን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት

ዳግመኛ ተወልዶ የዘላለም ህይወት እንደሚያገኝ እናምናለን።[6]

4. ደህንነት

ሰው ከፈጣሪው ጋር ለመታረቅ፣ ከኃጢአትና ከዘላለም ኩነኔ ለመዳን የሚችለዉ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት በቀራንዮ

መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ በሦስተኛዉ ቀን ከሙታን በተነሳው በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን

ብቻ እንደሆነ፣ ይህም ደህንነት ፍጹም ነፃ የሆነ የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ መሆኑን፣ የወንጌልን የምስራች የሰሙትም

በንስሐና በእምነት ክርስቶስ ኢየሱስን ሲቀበሉት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ዳግመኛ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች

ሆነው የዘላለም ህይወት እንደሚወርሱ እናምናለን።[7]

5. ቅዱስ ስርዓቶች፦

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ይጠብቁትና ያደርጉት ዘንድ በሰጣቸው ቅዱስ ስርዓቶች

እናምናለን። እነርሱም፥

o የውኃ ጥምቀት፦ የውሀ ጥምቀት ሰው ደህንነትን የሚያገኝበት ስርዓት ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ

አምነው የዳኑ በግል ወሳኔያቸው የሚፈጽሙት እንደሆነና ይህም ጌታን በማመን ያገኙትን ደህንነት

በሚታይ ሁኔታ ለመመስከር የሚፈፀም ስርዓት እንደሆነ እናምናለን።[8]

o የጌታ እራት፦ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ዕለት መስዋዕት አድርጎ ላቀረበው ስጋውና

ለኃጢአታችን ላፈሰሰው ደሙ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ እንደ ሰጠና ይህም የደህንነት ማግኛ ሳይሆን የጌታ

መታሰቢያ ብቻ እንደሆነ እናምናለን።[9]

6. ቤተክርስቲያን፦

o ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን፦ ኢየሰብ ክርስቶስ በመሰረታትና ራስ በሆነላት አምነው ያንቀላፉትን

አሁንም በጌታ ያሉትንና እንዲሁም ወደፊት ጌታን በመቀበል የሚድኑትን ሁሉ ባቀፈች ለሰው ዓይን

በማትታየው አንዲት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።[10]

o አጥቢያ ቤተክርስቲያን፦ ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸዉ አድርገው በመቀበልና ንስሐ በመግባት

ዳግመኛ ተወልደው መንፈስ ቅዱስ የጌታ አካል ያደረጋቸዉና ቃሉን በመታዘዝ እራሳቸዉን ለጌታ

አስገዝተዉ የሚኖሩ ምዕመናን ባሉባት በአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን እናምናለን።[11]

7. ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ፦

ኢየሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዷ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ራስ በመሆኑ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ራሷን የመምራትና

የማስተዳደር ሥልጣንና መብት እንዳላት እናምናለን።[12]

8. የክርስቶስ ዳግመኛ ምፅአት፦

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሺህ ዓመት መንግስቱ በፊት ዳግመኛ በክብር እንደሚመለስ የርሱ የሆኑትንም በክብር ወደ

ራሱ የሚሰበሰብበት የአማኞች ታላቅ ተስፋ በመሆኑ ቤተክርስቲያን ነቅታ በቅድስና የምትጠብቀው እንደሆነ

እናምናለን።[13]

9. ትንሣኤ ሙታን፦

ኢየሱስ ክርስቶስ በማይሞትና በከበረ አካል ከሙታን ተለይቶ በመነሳቱ በተገኘው ትልቅ ተስፋ በጌታ ያንቀላፉት በክብርና

በማይጠፋ አካል እንደሚነሱና ኃጢአተኞችም በአካል ትንሣኤ ወደ ዘላለም ፍርድ ቅጣት እንደሚሄዱ እናምናለን።[14]

ዋቢ ጥቅሶች

[1] ፪ኛ ጢሞ. ፫፥፲፮-፲፯፤ ፪ኛ ጴጥ. ፩፥፲፱-፳፩፤ ኢያ. ፩፥፰፤ ፩ኛ ተሰ. ፪፥፲፫፤ ፪ኛ ሳሙ ፳፫፥፪፤ መዝ. (፲፪)፥፮፤ ማቴ.

፳፬፥፴፭

[2] ዘፍ. ፫፥፳፪፣ ፲፯፥፩፤ ዘዳ. ፮፥፬-፭፤ መዝ. (፺)፥፪፤ መዝ. (፻፴፪)፥፯-፲፪፤ ኢሳ. ፵፥፳፰፣ ፵፷፥፲፪-፲፮፤ ሚል. ፫.፥፮፤ ዮሐ.

፲፯፥፳፬

[3] ዘፍ. ፫፥ ፩-፳፬፤ ዮሐ. ፫፥፲፮፣ ፩፥፲፪-፲፫፤ ማቴ. ፭፥፵፰፤ ኤፌ. ፬፥፮

[4] ዮሐ. ፩፥፩-፭፤ ሉቃ. ፩፥፳፮-፴፭፤ ቆላ. ፪፥፱፤ ዮሐ. ፫፥፲፬፤ ሮሜ ፭፥፰-፲፩፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳-፳፪፤ ሐዋ. ፩፥፩-፱፤

፪፥፴፪-፴፮፤ ዕብ. ፲፥፲፪፤ ዕብ. ፯፥፲፭-፳፭፤ ፩ኛ ዮሐ. ፪፥፩፤ የሐዋ. ፩፥፲-፲፩፤ ራዕ. ፩፥፮-፯፤ ሉቃ. ፲፥፵፪-፵፫

[5] ሐዋ. ፭፥፫-፬፤ ማቴ. ፳፰፥፲፱-፳፤ ሐዋ. ፲፮፥፯፤ ሮሜ ፰፥፱-፲፤ ዘፍ. ፩፥፳፫፤ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲-፲፪፤ ዮሐ. ፲፭፥፳፮-፳፯፤

፲፮፥፯-፲፭፤ ኤፌ. ፩፥፲፬፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩

[5 ሀ] ዮሐ. 3፥5-6 ፤ 16፥8 ፤ ቆሮ. 12 ፥ 13 ፤ ሮሜ 8፥14-16 ፤ ኤፌ. 1፥13-14፤ ገላ. 5፥22-23 ፤ 1 ቆሮ. 12፥3

[5 ለ] ሐዋ. 2፥4 ፤ 10፥44-46 ፤ 19፥6 ፤ 1፥5 ፤ 1፥8 ፤ 2፥39

[5 ሐ] 1 ቆሮ. 12፥4-11 ፤ ሮሜ 12፥4-11 ፤ ኤፌ. 4፥8-14

[6]ዘፍ.፩፥፳፮፤ ፫፥፩-፳፩፤ ሮሜ ፭፥፮-፲፬፤ ሐዋ. ፬፥፲፪፤ ዮሐ. ፫፥፭-፮፤ ፫፥፲፬-፲፰

[7] ቆላ. ፩፥፳፤ ፩ኛ ጢሞ. ፪፥፭-፮፤ ሮሜ ፫፥፳-፳፮፤ ፭፥፮-፲፩፤ ፮፥፳፫፤ ኤፌ. ፩፥፫-፲፬፤ ፪፥፰-፱፤ ዕብ. ፱፥፳፭-፳፰፤ ዮሐ.

፩፥፲፪-፲፫፤ ፫፥፫-፲፰፤ ቲቶ ፫፥፭-፯

[8] ማቴ. ፳፰፥፲፱፤ ሮሜ ፮፥፩-፬፤ ሐዋ. ፰፥፴፮-፴፱

[9] ሉቃ. ፳፪፥፲፬-፳፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፳፫-፴፪፤ ሐዋ. ፪፥፵፪

[10] ኤፌ. ፩፥፳፪-፳፫፤ ቆላ. ፩፥፲፰፤ ራዕ. ፲፱፥፯-፰

[11] ፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፲፪-፳፫፤ ገላ. ፫፥፳፮፤ ኤፌ. ፭፥፳፫-፳፮፤ ፩ኛ ጴጥ. ፪፥፱-፲

[12] ኤፌ. ፩፥፳፪፤ ቆላ. ፩፥፲፰